እውነተኛ የአካባቢ መጠርያ ስያሜዎችን በምናብ በተሳሉ ገፀ-ባህሪያት የተዋዙ ታሪኮች 

ክፍል ፭

ተረት ሰፈር እና ያልፈረሱት እውነታዎቿ

       

       ከለገሃር ወደ ፒያሳ በሚያሻግር ታክሲ ውስጥ ነኝ፡፡ ሹፌሩ ከአበባ መትኪያነት ለጥቂት የተረፈች የምትመስል HAICE ታክሲውን እንደ ህፃን ልጅ አባብሎ አስነስተቷት መንቀሳቀስ ጀምራለች፡፡ የታክሲዋን መነሳት ያላመነ የሚመስለው ወያላ እጁ ላይ የቀረውን ሳንቡሳ ጠቅልሎ ወደ አፉ በመክተት እንደነከሰ ካሴት በሚንተፋተፍ ደምጽ “ ፒያሳ….ፒያሳ…አንድ ሰው ፒያሳ” እያለ መጣራቱን ቀጥሏል፡፡ ቀጭን ነው! ከቅጥነቱ የተነሳ የጎረሰው ሳንቡሳ ወደ ጉሮሮው ሲወርድ ምስሩ ይታያል፡፡

 

ከእኔ ጀርባ የተቀመጡ ጥንዶች ከድንበር ግጭት የማይተናነስ ፅብ ውስጥ ናቸው፡፡ የፀባቸው መነሻ እሷ“ የአስር ሺህ ብር ሒውማን ሔር ካልገዛህልኝ” ሲሆን፤ አሱ ደግሞ “ አስር ሺህ ብር እንኳን ለሂውማን ሔር  ለሂውማን ራይትም አልተመደበም” በሚል ኢኮኖሚያዊ የሀሳብ ልዩነት ነው፡፡ ለነገሩ ፀሀይ ስትወጣ “አቃጠለችኝ!”፤ ዝናብ ሲመታን “ደበደበኝ!” እያልን ለፀብ ከምንጋበዝ ማህበረሰቦች አንፃር እንዲህ አይነት ፀብ በአሳማኝ ምክንያት ላይ የተመረኮዘ ይመስላል፡፡ተሳፋሪው ሬዲዮ ላይ ያለማቋረጥ የሚለፍፈውን የአበበ ግደይን የኳስ ትንታኔ አዘግቶ የጥንዶቹን የቃላት ጦርነት ይኮመኩማል፡፡ በጦርነቱ መሀል ድንገት መውረጃው የደረሰ ተሳፋሪም ጫፍ በሌላት ዓለም ላይ “ጫፍ ወራጅ!” እያለ ሌላውን ተክቶ ይወርዳል፡፡ በስንት ምክርና ተግሳፅ የተነሳችው ታክሲ ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤትን አልፋ የቸርችልን ዳገት መውጣት ስትጀምር ትኩሳቷ ተነሳባት ፡፡ ሹፌሩ እንደምንም እያባበለ ቴዎድሮስ አደባባይ ጋር ሲደርስ አርቄ ይሁን ውሃ ያለየለት ኮዳ አንሰቶ ራዲያተሯን ለማቀዥቀዝ ወረደ፡፡

 

       በመውረድና በመታገስ መሃል ሆኜ እያመነታው በመስኮት አሻግሬ ወደ ውጪ መመልከት ስጀምር እምዬ ተረት ሰፈር በፍርስራሾች መሀል ሆና ከፊቴ ቆማለች፡፡ በዚህ ቅፅበት የልብ ወዳጁ ሞቶ አልቅሶ ለመቅበር እንዳልታደለ ምስኪን ስደተኛ ውስጤን ባርባር አለው!!!  ከፍርስራሾቿ መሀል ደራሲ በዓሉ ግርማ “ደራሲው” በሚል ልቦለዱ  በምዕናቤ የቀረፃቸው መቼቶችና ገፀ ባህሪያት አእምሮዬ ውስጥ መመላለስ ጀመሩ፡፡ በተለይም በልቦለዱ ውስጥ በዋና ገፀባህሪነት የተሳለው የግሃዱ ዓለም ጋሽ ስብዓት ገ/እግዚያብሔር፡፡ተረት ሰፈር ከጋሽ ስብኣት ህይወት ጋር በአያሌው የተቆራኘች መንደር ነበረች፡፡ አብዛኛውን የህይወት ዘመኑን በዚችው መንደር ውስጥ ኖሮባታል፡፡ የአብዛኞቹ አጫጭር ልቦለዶች መነሻ ሀሳቦቹም ከዚህች መንደር የኑሮ ዘይቤ ውስጥ የተቀዱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- “የሞትና አጋፋሪ እንደሻው” ጥንስስ የሆኑት የተረት መንደሯ እማሆይ ጣዲቄን ማንሳት ይቻላል፡፡

በተረት ሰፈር እውነታዎች ውስጥ  ከስሟ ጋር አብረው ከሚነሱ  እንቁዎቿ መሀል ሌላኛው  የሳቁ ንጉስ ኮሜዲያን ተስፋዬ ካሳ  ነው፡፡ ተስፍሽ በህይወት ዘመኑ ያበረከታቸውን የኮሜዲ ስራዎች መለስ ብለን በንቃኛቸው በአብዛኛው በራሱ እና በቤተሰቡ ላይ በሚያተኩሩ ቀልዶች የተከሸኑ ናቸው፡፡ በእሱ ቤተሰብ ውክልና ውስጥ የተረት ሰፈርን ውሎና ዳር የአብሮ አደግነት ስሜት እስኪሰማን በአእምሮአችን ስሏት አልፏል!!! ይቺ ታሪከኛ ሰፈር ስያሜዋን ያገኘችው በአዲስ አበባ ከተከፈቱት የመጀመሪያዎቹ ሆቴሎች አንዱ በነበረው በሆቴል ዳፍራስ ባለቤት በፈረንሳዊው ሙሴ ቴረስ ስም እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሰውየው በዘመኑ ከነበረው እውቅና የተነሳ ስሙ በአካባቢዋ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠሩ በተለምዶ ቴረስ ሰፈር እየተባለች ቆይታ ቀስ በቀስ ስያሜዋ በአማርኛ ቃላቶች አሟሽታ ወደ ተረት ሰፈርነት ተሸጋግራለች፡፡ ምንም እንኳን  ዛሬ ላይ በልማት ሰበብ ታርሳና ተምሳ  ለቁራሌው ተላልፋ ብትሰጥም፤ በፍርስራሾቿ ውስጥ ሊቀበር የማይችል የብዙ ሰው ትዝታዎችን በውስጧ ይዛለች፡፡ ከሰይጣን ቤት  ጀምሮ ላም ሰፈር፣ አበባ ሰፈር፣ ጎርደሜን የመሳሰሉ መንደሮቿ  ከነጫማ ሰፊው ጋሽ ከበደ አይነት እንቁዎቿ ጋር በእኔ አይነቱ አልፎ ሒያጅና  በነዋሪዎቿ አንደበት ስቅ እስኪላት ድረስ ስትዘከር ትኖራለች፡፡

      በመስኮት አሻግሬ እንደቀልድ  ከነጎድኩበት የተረት ሰፈር ትዝታዪ መሃል “ፍሬንድ መጨረሻው  ነው!” የሚል የወያላው ድምጽ ድንገት ስቦ አነቃኝ፡፡ ደንግጬ ዙሪዬን ስቃኝ የተሳፈርኩባት ታክሲ ፒያሳ ደርሳ እኔና ወያላው ብቻ ተፋጠን ቀርተናል፡፡ ከደቂቃዎች በፊት በሒውማን ሔር ሰበብ የተጀመረው የቃላት ጦርነት በምን ተቋጨቶ ይሆን?? እኔ ሳላይ የሰላም ሚኒስቴር ጣልቃ ገባ? ወይስ ጥንዶቹንም እንደ ተረት ሰፈር በልማት አነሷቸው??

 

 

                                                                    /////ይቀጥላል//////  

©2018 BY AFETARIK.