እውነተኛ የአካባቢ መጠርያ ስያሜዎችን በምናብ በተሳሉ ገፀ-ባህሪያት የተዋዙ ታሪኮች 

ክፍል ፫

ውሎ አዳር በሀዲድ ገበያ

 

   “ የሀዲድ ገበያን ያላየ ኤግዚቢሽን ባዛርን ያመሰግናል ” ይላሉ  ስማቸውን ያልያዝኩት አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፡፡


   ወዳጄ ሆይ…. እግር ጥሎህ ስቴዲየም አካባቢ ከተገኘህና ጥላሁን አደባባይ ጋር ደርሰህ ቀና ስትል በሸራ ተወጣጥረው  የቆሙ የአቡ ወለድ ካርቶን የሚያካክሉ ቤቶች ካየህ እመነኝ ያለኸው ሀዲድ ገበያ አቅራቢያ  ነው፡፡ ተከተለኝ……..

   ሀዲድ ገበያ የተቆረቆረችው በእምዬ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት እንደሆነ በአፈ-ታሪክ ደረጃ ይነገራል፡፡ እሳቸው  ከጅቡቲ እስከ ለገሀር ባዘረጉት የባቡር ሀዲድ ሊይ መተዳደሪያዋን ያደረገችው ሀዲድ ገበያ ዛሬ ላይ አቋርጧት የሚያልፍ ባቡር ባይኖርም ፆሟን አታድርም፡፡ በእምዬ ተቆርቁራ በልማት ተሸራርፋ እየተንገታገተች እዚህ ብትደርስም እጅ አልሰጠችም፡፡ ዛሬም ድረስ እጅሽ ከምን ላላት ከሳልባጅ እስከ አዳዲስ አልባሳት፤ ከተባይ ማጥፊያ እስከ ብጉር ማጥፋፊያ፤ ከፍራፍሬ እስከ ቁንዶ በርበሬ፤ ከጎመን ዘር እስከ ሳኒታይዘር … ብቻ ምን አለፋህ መዲናዋ ላይ እግርህ እስኪቀጥን ድረስ ፈልገህ ያጣኸውን ነገር ሁሉ ቆጣጥራ ባልጠበከው ዋጋ እነሆ በረከት ትልሃለች፡፡

   መሃል ሸገር ላይ ይገኛል ብለህ የማትገምተው የከብቶች ኩበት እንኳን በክብር ተመዳድቦ የምታገኘው ሀዲድ ገበያ ላይ መሆኑን ስነግርህ በኩራት ነው፡፡በዚህች ገበያ ላይ የማይታደም የማህበረሰብ ክፍል የለም፡፡ ከሎተሪ አዟሪ እስከ ደንብ አልባ ደንብ አስከባሪ፤ ከሰርቶ አደር እስከ ለክፎ አደር፤ ከሬሳ ሳጥን ደላላ  እስከ ቅስም የለሽ ሌባ ድረስ የእለት ጉርስ የሚያገኝባት ቦታ ነች፡፡ ምናልባት ቅስም የለሽ ሌባ ስል ግራ ከገባህ  ምን አይነት መሰለህ… ለምሳሌ ኪስህ ገብቶ ስልክህን እያወጣ እጅ ከፍንጅ በትይዘው “ ቻርጅ ላረግልህ  ነው” ብሎ ድርቅ የሚል ሌባ ወይም ደግሞ የሚሰረቅ ነገር ባይኖርህ  እንኳን ሀሳብህን ሰርቆ አላየሁም የሚልህ፡፡


   ሀዲድ ገበያ ላይ ከግብይት ባሻገር ልትታዘበው የምትችለው ሌላ ብዙ ገፅታዎች አሏት፡፡ ለምሳሌ፡- “መዳን በሌላ የለም.. እንድንበት ዘንድ…..” እያለ ገበያ መሃል ቆሞ ከሚመሰክር ወንጌላዊ ጀምሮ በደርግ ዘመን አእምሮውን ከሳተ እና “ኢትዮጵያ ትቅደም!” እያለ በወታደራዊ ሰላምታ አቀባበል እስከሚያደርግልህ ጎልማሳ ድረስ ልትመለከት ትችላለህ፡፡ በዚህ አጋጣሚ የትኛውም ሰው ያለ ማንም ከልካይ ሀሳቡን በነፃነት እንዲገልፅ በመፍቀድ ሀዲድ ገበያ ከሎንዶኑ Hyde park ቀጥሎ ሁለተኛ ትመስለኛለች፡፡
ከኑሮ እኩል የምትለበልበው ፀሀይ ተራዋን ለጨረቃ ለቃ ማዘቅዘቅ ስትጀምር ሀዲድ ገበያም መደቧን ሰብስባና ሸራዋን አሳስራ ለሌላ ንግድ ትሰናዳለች፡፡ ዙሪያዋን የከበቧት ዉትፍታፍ ጎጆዎች በራፋቸውን ወለል አድርገው የካቲካላ ደንበኞቻቸዉን  መጠባበቅ ይጀምራሉ፡፡ ከመጠጥ ጋር የሴት ልጅ ክቡር ገላ እንደሸቀጥ ለገበያ ይቀርባል፡፡ ይህን ውሎና አዳሯን የታዘበ አንድ አዝማሪ እንዲህ ብሎ ተቀኝቶላታል ይባላል፡፡  ለዛሬ እኔም አንተም ሳይመሽብን በዚህች ስንኝ እናብቃ…..


የሀዲድ ገበያ በጠዋት ቀንቶኛል   
ሽንኩርትም ጎመንም ገዛው ይበቃኛል

ያመሸው እንደሆን  ደግሞ ስጋ ያምረኛል……                                                                                            

                         /////// ይቀጥላል ////////                     

©2018 BY AFETARIK.