እውነተኛ የአካባቢ መጠርያ ስያሜዎችን በምናብ በተሳሉ ገፀ-ባህሪያት የተዋዙ ታሪኮች 

ክፍል ፮

አበዳሪዬን ጥበቃ በዶሮ ማነቂያ

ፎቶ በአድሪያኖ ማርዚ (Metamorfose Ambulante)

www.adrianomarzi.com

              “ብድርን የማረሳሳት ጥበብ” የምትል አንዲት ደርባባ መፅሀፍ ፅፌ ብጨርስም ለማሳተም እጅ አጠረኝ፡፡

ይሔን በማንም ደራሲ ያልትደፈረ እምቅ ሀሳቤን ለወገኔ ለማካፈል ካለኝ ጉጉት የተነሳ አበዳሪ መፈለግ ጀመርኩ፡፡ በነገራችን ላይ ከሞት በኋላ ስማችን በሰዎች ዘንድ ሁሌ እንዲታወስ ከሚያስችሉን ጥበቦች አንዱ ብድር መበደር ነው፡፡

     ጥሎ የማይጥለው የጥበብ አምላክ ረድቶኝ ከአያሌ ያልተሳኩ ሙከራዎች በኋላ ከአንድ ወዳጄ እርጥብ ኪስ ላይ ጣለኝ፡፡ ገና ለምን እንኳን እንደፈለኩት ሳይጠይቀኝ ከእኔ በላይ እሱ ሊያገኘኝ እንደጓጓ በሚያስታውቅ ደምፀት ፒያሳ ላይ እንድንገናኝ ቀጠሮ አስይዞኝ ስልኩን ዘጋው፡፡ በዚህ ቅፅበት የተሰማኝ ደስታ በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሬ የመጀመሪያውን ወር ደሞዝ ከበላው ቀን ጀምሮ  እስካሁኗ ሰዓት ድረስ አይቼው የማላቀው ነው፡፡

ለወራት በሬን ዘግቼ አምጬ የወለድኳት የበኩር ስራዬ ከተደራሲው እጅ ገብታ ብዙዎች ለዘመናት ከተጨነቁበት ውዝፍ እዳዎቻቸው ተፈውሰው፤ የብድር እስራታቸው ሲፈታ በአይነ ህሊናዬ እየመጣ በደስታ ሰከርኩ፡፡ከወዳጄ ጋር ወደ ተቀጣጠርኩበት ፒያሳ የደረስኩት ከቀጠሮአችን ሁለት ሰዓት አስቀድሜ ስለነበር አንድም እሱ እስኪመጣ፤ በዛውም በባዶ ሆድ ብድር መጠየቅ አበዳሪን መናቅ ነው ብዬ ምላስ ሰንበር ፍለጋ ወደ ዶሮ ማነቂያ ጎራ አልኩኝ፡፡ መቼም የኔ አይነቱ ደሀ ጥሬ ስጋ በላ የሚባለው ምላሱን ሲነክስ ብቻ!!!

   የጥንቷ ደጃዝማች አፍወርቅ መንደር የአሁኗ ዶሮ ማነቂያ እንደወትሮዋ ሁሉ ዛሬም በስጋ ቤቶቿና በስጋ ስፔሻሊስቶቿ ተከባ እንደደራች ነው፡፡ ነጫጭ ጋዎናቸውን ሽክ ያሉት የስጋ ስፔሻሊስቶች  በእነ ፋሲካ፣ ቤቴልሔም፣ በቀለ፣ ባንቡ፣ ደምሴና አዱኛን በመሳሰሉ የስጋ ቤት በራፎች ላይ ተደርድረው ቢላዎቿቸውን ያለ እረፍት ካራቴ እያጫወቷቸው የእንኳን ደህና መጣቸው ትርኢት በማሳየት ተጠምደዋል፡፡ በትርኢቱ መሀል አላፊ አግዳሚውን በፈገግታ እየቃኙ “ ወንድም … ጎራ በያ.. “ የምትል አጠር ያለች ማስታወቂያ  ወርወር ያደርጋሉ ፡፡ ጎራ ላለው ሁሉ የዱቤ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ይመስል.. ከስጋ ቤቶቿ ወረድ እንደተባለ ሌላ ትርኢት ይቀጥላል፤

 

በለውዝ አዟሪዎችና በጫት ነጋዴዎች የተከበበ፡-

የባህርዳር፣ የገለምሶ፣ በለጬ፣ አወዳይ፣አቦ ሚስማር እያለ የሚቀጥል የጫት ሬሳ!!! በዚሀ ቦታ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣ ሰው ይሔ ሁሉ ቅጠላ ቅጠል ለእለት የጥርስ ፍጆታ የሚውል ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ለቀጣዩ ክረምት ለመትከል  ያስፈሉት ችግር ሊመስለው ይችላል፡፡ እውነታው ግን እምዬ ዶሮ ማነቂያ ለችግኝ  ቦታ የላትም!

 

     ከእነዚህ ቅሞ ማሳያ ቤቶች መሃል ግድግዳውን ታከው “ኑ ቡና ጠጡ” በሚል የወረቀት ማስታወቂያዎች የታጠሩ የጀበና ቡና መሸጫዎች ሌላኛው የዶሮ ማነቂያ ድምቀቶች ናቸው፡፡ ከመንታ መንገድ ጀምሮ በብቅ እንቅ፣ በሹፌር ሰፈር፣ በአንፒር፣ በድሮ መዘጋጃ፣ በግንብ አጥር ወ.ዘ.ተ.. መንደሮቿ ውስጥ ቢወጡ ቢወርዱ እነዚህን የጀበና ቡናዎች በየሁለት እርምጃዎች መሃል ተራምዶ ማለፍ ግድ ይላል፡፡

 

      ይቺን እድሜ ጠገብ ሰፈር ከሌሎች የመዲናዋ አካባቢዎች ለየት ከሚያደርጓት መገለጫዎቿ አንዱ የጥንታዊቷ አዲስ አበባ ኪነ ህንፃዎች ባለቤት መሆኗ ነው፡፡ ከአፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት ጀምሮ እንደተገነቡ የሚገለፅላቸው እፁብ ድንቅ የሆኑ ኪነ ህንፃዎቿ ዛሬም ድረስ እርጅናን ተቋቁመው በኩራት እንደቆሙ ናቸው፡፡ በቅርስነት ተመዝግበው ዛሬም በእማኝነት  ከቆሙት ህንፃዎቿ መሀል የመጀመሪያው ኢትዮጵዊ የህክምና ባለሙያ የነበሩት የሀኪም ወርቅነህ መኖሪያ ቤት እና የመጀመሪያውን የመዲናዋ መዘጋጃ ቤት ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

 

   በነገራችን ላይ ዶሮ ማነቂያ ውስጥ በኑሮ ውድነት ተማሮ ራሱን ያጠፋም ፤ ብድር ባለመክፈል ስቅላት ተፈርዶበት ታንቆ የሞተም  ዶሮ ከእድር መዝገቧ ላይ አልሰፈረም፤ መንደሯ ዛሬ ለምትጠራበት ስያሜ መክንያት የሆናት ከዶሮ ይልቅ  ሰው የማነቅ ተግባሯ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ በእምዬ ምኒሊክ ተጀምሮ በቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስትም ቀጥሎ በነበረው የፍርድ ሒደት ስቅላት የተፈረደባቸው ሰዎች ቅጣታቸው የሚፈፀመው በዚች ቦታ ላይ ነበር ይባላል፤ በዛ የተነሳ የድሮ ሰው ማነቃያ እየተባለች ቆይታ  በጊዜ ሒደት አሁን ለምትጠራበት ስያሜ በቅታለች፡፡

      የዶሮ ማነቂያን ታሪክ ከቀረበልኝ ምግብ  ጋር አጣጥሜ ከቤትኪራይ የተረፈችኝ ድፍን የመቶ ብር ኖት መዘዝ አንዳድርኩ በጉጉት ስጠብቀው የነበረው ወዳጄ ደወለ፡፡ እሱ መሆኑን ሳውቅ በቀጠረኝ ሰዓት የተሰማኝ  ደስታ ስሜት ዳግም አገረሽብኝ!! አበዳሪ ወደ ተበዳሪ ደውሎ “የት ነህ?” የሚልበት ዘመን በመምጣቱ ፈጣሪዬን ለማመስገን ወደ ላይ ቀና አልኩኝ፡፡ በዚህ ቅጽበት ከምስጋናዬ የገዘፈ አንዳች ምህታታዊ ትውስታ ወደ ውስጤ ብልጭ ብሎ ባለውበት በረዶ ሰራው፡፡ ለካስ ይህ ወዳጄ ያለመክንያት ከእኔ በላይ ሊያገኘኝ አልጓጓም፡፡ ብድር አለብኝ! አዎ ብድር አለብኝ!!  ከወራት በፊት እግሩ ላይ ተጎዝጉዤ የተቀባበልኩት ብድር፤ ደሞዝ ሲወጣ ልከፍል ከደሞዜ በላይ የተበደርኩት ብድር….!!!

     

     ይህ ሰው ያለ አንዳች መክንያት ዶሮ ማነቂያን ለቀጠሮ አላጫትም፡፡ ማን ያውቃል? ለዘመናት ተቋርጦ የነበረውን የሰቅላት ፍርድ በእኔ ለማስቀጠል ሰይጣን ገመድ አስይዞ ልኮት ቢሆንስ?? ማን ያውቃል?? የበላውበት እጄን ሳላለቀልቅ ደርቄ በተቀመጥኩበት ስልኬ ለሁለተኛ ጊዜ መጨው ጀመረች፡፡

                                                   

 

                                                          ////// ይቀጥላል////

©2018 BY AFETARIK.