እውነተኛ የአካባቢ መጠርያ ስያሜዎችን በምናብ በተሳሉ ገፀ-ባህሪያት የተዋዙ ታሪኮች 

ክፍል ፪

ድድ ማስጫ እና የሚሰጡ ድዶች  

      ወዳጄ ሆይ.. ባለፈው ስለ ማርገጃ ትዝታዬ የሆድ የሆዳችንን ስንጨዋወት ካቆምንበት እንደምንቀጥል ቃል መግባቴን አትዘነጋውም አይደል? እነሆ ቀጥለናል…

     ጨርቆስ ውስጥ የገባ ሰው ቶሎ የማይወጣበት ሁለት መክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው የነዋሪዎቿ ጣፋጭ ጨዋታ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከማስተር ፕላን ነፃ የሆነው ጉራንጉር መንገዷ የገባህበትን ስለሚያስጠፋ ነው፡፡ እነሆ እኔም እንደ ኑሮ ከተወሳሰበው መንገዶቿ መሃል አንዱን ይዤ  በታሪከኛዋ ፈለገ ዮርዳኖስ ት/ቤት (ፈሌ) በኩል ብቅ ብዬ  ስለ ድድ ማስጫ  ትንሽ ላጫውትህ ወደድኩኝ፡፡

      ድድ ማስጫ ይሔን ስያሜዋን ያገኘችው በገዛ ተግባሯ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ በዚህች ቦታ ላይ የሪቼ ልጆች ብትል የአልጋ ተራ፣ የኮረፌ ተራ፣ የቆሎ ተራ፣ የዲተል በር፣ የማርገጃ፣  የቁራ ግቢ፣ የዜሮ ዘጠኝ፣ የጀርመን መስጊድ፣ የሱማሌ መስጊድ፣ የፖሊስ ሰፈር፣ የሽቦ ግቢ፣ የሲሳይ ሜዳ፣ የጨነቀ ሱቅ፣ የመንታ ሱቅ፣ የአሸዋ ተራ፣ የፖፖላሬ፣ የምድር ባቡር፣ የዶርዜ ሰፈር ልጆች….. ብቻ ምን አለፋህ ድዳቸውን ሳያሰጡ ያደጉባት ጥቂት ናቸው፡፡ ምን እነሱ ብቻ! ከዬትኛውም የሀገሪቷ ከተሞች መጥቶ መድረሻዉን ጨርቆስ ላይ ያደረገ የክፍለ ሀገር ልጅ ከሸገር ጋር የመጀመሪያውን ትውውቅ የሚያደርገው እዚችው ድድ ማስጫ ላይ ነው፡፡

      ድድ ማስጫ በተለይ ለጨርቆስ ልጆች ውለታዋ ክፍ ያለ ነው፡፡ ንጋት ላይ ህፃኑ ጨርቆስን ተሳልሞ የመጣውም፤ ሲጎነጭ (ሲቸልስ) አድሮ ከነ ሀንጎቨሩ የተገኘውም  ሰውነቱን በፀሀይ፣ ምላሱን በነቆራ የሚያፍታታው  ድድ ማስጫ ላይ ነው፡፡ ቋሚ ደንበኛ ሆነህ በቦታው ላይ ከተገኘህ ከፀብ ጋር ፀበኛ በሆነ ነቆራ ጥርስህን ለምች አጋልጠህ በሳቅ ስትነፍር ትውላለህ፤  አቴንዳንስ ላይ ከሌለህም ስቅ ባለህ ቁጥር  ድድ ማስጫ ላይ እየተቦጭክ መሆኑ ይገባሃል፡፡ ለምሳሌ አንዱ መጥፋትህ ያሳሰበው ይመስል በቅጽል ስምህ አንስቶህ የት እንደጠፋህ ይጠይቃል፤ ሌላው ቀጠል ያደርግና “ አልሰማህም እንዴ?! ከሱስ የመውጫ መንገዶች” የሚል መፅሃፍ ሊፅፍ ግማሽ ገለምሶ ይዞ ገባ እኮ”” ሌላው ይከተላል፡- “ምን አለ በለኝ አሁን መታ መታ ሲያደርግ ርዕሱን ቀይሮ “የምርቃና ጥበብ” ይለዋል”ቂቂቂቂቂ….. ጨዋታው በዚህ መልክ ይደራል፡፡

       ድሮ ድሮ የሰፈሯ ልጆች የህንድ ፊልሞችን ከማየት አልፈው የመተርጎም ብቃት ላይ የደረሱ ነበሩና ለምን ትናንትና ያየኀው ፊልም አይሆንም ጠዋት ጆሮህ እስኪግል ድረስ ይገረብልህ (ዳግም ይተረክልህ) ነበር፡፡ አሁን ላይ ይሄ የለም፤ የዛሬዋ ድድ ማስጫ ከእንግሊዝ ፕሪሜርሊግ እስከ ሴሪኤ የሚሻገሩ የእግር ኳስ ተንታኞችን በማምረት ተጠምዳለች፡፡ ምናልባት የምትውደው ተጨዋች ጠዋት ምን እንደበላ ለማወቅ ከጓጓህ እድሜ ለድድ ማስጫ! እንኳን የበላውን የሚበላውን ትተነብይልሃለች፡፡

    በድድ ማስጫ ላይ የሚነሱ ርዕሰ ጉዳዮች ብዙ ናቸው፡- ፖለቲካው፣ ማህበራዊው፣ ፍልስፍናው … ሁሉም አሉ፡፡ በፖለቲካው ዘርፍ፡-ከንጉሱ ዘመን ውሎና አዳር፤ እስካሁኑ መንግስት የፖለቲካ ምህዳር  የዘለቀን ግላዊ አስተያየቶች ታስተነግዳለች፤ በማህበራዊው፡- ከስራ ማጣት እስከ ልማት ተነሺነት ስጋት ያሉ ብሶቶችን ባለመታከት ስታዳምጥ ታረፍዳለች፡፡ በፍልስፍናውም በኩል ማን ብሏት! ለምሳሌ:- አንዱ ተነስቶ “አዳም ከገነት የተባረረው ችግኝ ነቅሎ ነው!” ሲል ልትሰማው ትችላለህ፤ ሌላው ቀበል አድርጎ “ለምን? እንዴት? ወዴት?” ሲል ምሳ ሰዓት ደርሶ ሁሉም ወደየመጣበት መበታተን ይጀምራል፡፡

     ወዳጄ… እኔም ወደመጣሁበት ከመመለሴ በፊት ለዛሬ እዚችው ድድ ማስጫ ላይ በሰማዋት ፍተላ ብሰናበትህስ? ሰፈር ውስጥ ለቅሶ ነበር አሉ፡፡ ይሔን ያልሰማ አንድ ጀለስ ጥንብዝ ብሎ ሲገባ አባቱ በቁጣ “አንተ ለምድነው የአቶ ከበደ ቀብር ላይ ያልሔድከው?” ሲሉት ምን ቢል ጥሩ ነው “መች ጠራኝ?”

                               

                                            /////// ይቀጥላል ////////

©2018 BY AFETARIK.